1 Kings 18

ኤልያስና አብድዩ

1ከብዙ ጊዜ በኋላም በሦስተኛው ዓመት እንዲህ የሚል የእግዚአብሔር ቃል ለኤልያስ መጣለት፤ “ሄደህ ለአክዓብ ተገለጥ፤ እኔም በምድሪቱ ላይ ዝናብ አዘንባለሁ።” 2ስለዚህም ኤልያስ ራሱን በአክዓብ ፊት ለመግለጥ ሄደ።

በዚህ ጊዜ ራብ በሰማርያ ክፋኛ ጸንቶ ነበር።
3አክዓብም የቤተ መንግሥቱን አዛዥ አብድዩን ጠራው፤ አብድዩም እግዚአብሔርን በጣም የሚፈራ ሰው ነበር። 4ኤልዛቤል የእግዚአብሔርን ነቢያት እያስገደለች በነበረበት ጊዜ፣ አብድዩ መቶውን ነቢያት ወስዶ አምሳ አምሳውን በሁለት ዋሻ ውስጥ ሸሽጎ እንጀራና ውሃ ይሰጣቸው ነበር። 5አክዓብም አብድዩን፣ “ተነሣና በአገሪቱ ውስጥ ወዳሉት ምንጮችና ሸለቆዎች ሂድ፤ ፈረሶቻችንና በቅሎዎቻችን እንዳይሞቱ በሕይወት እንዲቈዩ ምናልባት ሣር እናገኝ ይሆናል።” አለው። 6ስለዚህ የሚሄዱበትን ምድር ተከፋፈሉ፤ አክዓብ በአንድ በኩል፣ አብድዩም በሌላ በኩል ሄደ።

7አብድዩ በመንገድ ላይ ሳለም ኤልያስን አገኘው። አብድዩም ዐወቀው፤ ወደ መሬት ለጥ ብሎ እጅ በመንሣት፣ “ጌታዬ ኤልያስ ሆይ፤ በርግጥ አንተ ነህን?” አለው።

8እርሱም፣ “አዎን እኔ ነኝ፤ ሂድና ለጌታህ፣ ‘ኤልያስ እዚሁ አለልህ’ ብለህ ንገረው” ሲል መለሰለት።

9አብድዩም እንዲህ አለው፤ “ምነው ምን አጠፋሁና ነው ባሪያህ እንዲሞት ለአክዓብ አሳልፈህ የምትሰጠው? 10አምላክህን ሕያው እግዚአብሔርን! ጌታዬ አንተን ለመፈለግ መልእክተኛ ያልላከበት ሕዝብና መንግሥት የለም፤ የትኛውም ሕዝብ ሆነ መንግሥት አንተ በዚያ አለመኖርህን ባስታወቀው ጊዜ ሁሉ አንተን አለማግኘቱን ለማረጋገጥ ያስምለው ነበር። 11አሁን ግን አንተ ወደ ጌታዬ ሄጄ፣ ‘ኤልያስ እዚህ አለልህ’ እንድለው ትፈልጋለህ፤ 12ተለይቼህ ስሄድ የእግዚአብሔር መንፈስ የት እንደሚወስድህ አላውቅም፤ ታዲያ ሄጄ ለአክዓብ ከነገርሁት በኋላ ሳያገኝህ ቢቀር እኔን ይገድለኛል፤ ነገር ግን እኔ ባሪያህ ከጕልማሳነቴ ጀምሮ እግዚአብሔርን አመልካለሁ። 13ጌታዬ ሆይ፤ ኤልዛቤል የእግዚአብሔርን ነቢያት ባስገደለች ጊዜ ምን እንዳደረግሁ አልሰማህምን? መቶውን የእግዚአብሔር ነቢያት ወስጄ አምሳ አምሳውን በሁለት ዋሻ በመሸሸግ እህልና ውሃ ሰጠኋቸው። 14ታዲያ አንተ ሄጄ ለጌታዬ፤ ‘ኤልያስ እዚህ አለልህ’ እንድለው ትፈልጋለህ፤ እርሱም ይገድለኛል!”

15ኤልያስም፣ “በፊቱ የቆምሁት ሁሉን የሚገዛ ጌታ እግዚአብሔርን፣ ዛሬ በአክዓብ ፊት በርግጥ እገለጣለሁ” አለ።

ኤልያስ በቀርሜሎስ ተራራ ላይ

16ስለዚህ አብድዩ ሄዶ ይህንኑ ለአክዓብ ነገረው፤ አክዓብም ኤልያስን ለማግኘት ሄደ። 17ኤልያስንም ባየው ጊዜ፤ “እስራኤልን የምታውክ አንተ ነህን?” አለው።

18ኤልያስም መልሶ እንዲህ አለ፤ “አንተና የአባትህ ቤት እንጂ እኔ እስራኤልን አላወክሁም። የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ተዋችሁ፣ እነ በኣልንም ተከተላችሁ። 19አሁንም ሕዝቡ በቀርሜሎስ ተራራ እንዲገናኘኝ ለመላው እስራኤል ጥሪ አድርግ። ከኤልዛቤል ማእድ የሚቀለቡትን አራት መቶ አምሳውን የበኣል ነቢያት፣ አራት መቶውንም የአሼራ ነቢያት አምጣቸው።”

20ስለዚህ አክዓብ በመላው እስራኤል ጥሪ አደረገ፣ ነቢያቱንም በቀርሜሎስ ተራራ ሰበሰበ። 21ኤልያስም በሕዝቡ ፊት ቀርቦ፣ “በሁለት ሐሳብ የምትዋልሉት እስከ መቼ ድረስ ነው? እግዚአብሔር አምላክ ከሆነ እግዚአብሔርን ተከተሉ፤ በኣል አምላክ ከሆነም በኣልን ተከተሉ” አለ።

ሕዝቡ ግን አንዲት ቃል አልመለሱም።

22ከዚያም ኤልያስ እንዲህ አላቸው፤ “ከእግዚአብሔር ነቢያት የተረፍሁ እኔ ብቻ ነኝ፤ በኣል ግን አራት መቶ አምሳ ነቢያት አሉት። 23ሁለት ወይፈኖች ስጡን፤ እነርሱም አንዱን መርጠው ይውሰዱ፤ በየብልቱም ቈራርጠው፣ በዕንጨት ላይ ያኑሩት፤ ግን እሳት አያንድዱበት፤ እኔም ሁለተኛውን ወይፈን አዘጋጃለሁ፤ በዕንጨትም ላይ አኖረዋለሁ፤ እሳት አላነድድበትም። 24ከዚያ እናንተ የአምላካችሁን ስም ጥሩ፤ እኔም የእግዚአብሔርን ስም እጠራለሁ፤ ሰምቶ በእሳት የሚመልሰውም እርሱ እውነተኛ አምላክ ነው።”

ከዚያም ሕዝቡ ሁሉ፣ “ያልኸው መልካም ነው” አሉ።

25ኤልያስም ለበኣል ነቢያት፣ “እናንተ ብዙ ስለ ሆናችሁ በመጀመሪያ አንዱን ወይፈን መርጣችሁ አዘጋጁ፤ የአምላካችሁን ስም ጥሩ፤ ነገር ግን እሳት አታንድዱበት” አላቸው። 26ስለዚህ የተሰጣቸውን ወይፈን ወስደው አዘጋጁት። ከዚያም ከጧት እስከ እኩለ ቀን የበኣልን ስም ጠሩ፤ “በኣል ሆይ ስማን” እያሉ ጮኹ፤ ድምፅ ግን የለም፤ የሚመልስ አልነበረም፤ በሠሩት መሠዊያ ዙሪያም እየዘለሉ ያሸበሽቡ ነበር።

27እኩለ ቀንም ላይ ኤልያስ፣ “ድምፃችሁን ከፍ አድርጋችሁ ጩኹ እንጂ፤ አምላክ አይደለም እንዴ! ምናልባት በዐሳብ ተውጦ ወይም ሥራ በዝቶበት፣ አልያም በጕዞ ላይ ይሆናል፤ ተኝቶም ከሆነ ቀስቅሱት” እያለ ያፌዝባቸው ጀመር። 28ስለዚህ እየጮኹ እንደ ልማዳቸው ደማቸው እስኪፈስስ ድረስ ሰውነታቸውን በሰይፍና በጩቤ ያቈስሉ ነበር። 29እኩለ ቀን ዐለፈ፤ እነርሱም የሠርክ መሥዋዕት እስኪቀርብ ድረስ የሚዘላብድ ትንቢት ይናገሩ ነበር፤ አሁንም ድምፅ የለም፤ የመለሰና ከቁም ነገር የቈጠረውም አልነበረም።

30ከዚያም ኤልያስ ሕዝቡን በሙሉ፣ “ወደ እኔ ቅረቡ” አላቸው፤ ሕዝቡም ሁሉ ወደ እርሱ ቀረቡ፤ እርሱም ፈርሶ የነበረውን የእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ። 31ከዚያም ኤልያስ፣ “ስምህ እስራኤል ይባላል” ተብሎ የእግዚአብሔር ቃል በመጣለት በያዕቆብ ልጆች ነገድ ቍጥር ልክ ዐሥራ ሁለት ድንጋይ ወስዶ፤ 32በድንጋዮቹም ለእግዚአብሔር ስም መሠዊያ ሠራ፤ በመሠዊያውም ዙሪያ ዐሥራ አምስት ሊትር ውሃ
15 ሊትር ያህል ነው።
የሚይዝ ጕድጓድ ቈፈረ፤
33ዕንጨቱን ረበረበ፤ የወይፈኑንም ሥጋ በየብልቱ ከቈረጠ በኋላ፣ በዕንጨቱ ላይ አኖረው። ከዚያም፣ “ውሃ በአራት ጋን ሞልታችሁ፣ በመሥዋዕቱና በዕንጨቱ ላይ አፍስሱ” አላቸው። 34ደግሞም፣ “እንደ ገና ጨምሩበት” አላቸው፤ እነርሱም ጨመሩበት። “ሦስተኛም ጨምሩበት” ሲል አዘዛቸው፤ እነርሱም ለሦስተኛ ጊዜ ጨመሩበት። 35ውሃውም በመሠዊያው ዙሪያ ፈሰሰ፤ ጕድጓዱንም ሞላው።

36የሠርክ መሥዋዕት በሚቀርብበትም ጊዜ፣ ኤልያስ ወደ መሠዊያው ቀረብ ብሎ እንዲህ ሲል ጸለየ፤ “የአብርሃም፣ የይስሐቅና የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ የእስራኤል አምላክ መሆንህ፣ እኔም የአንተ አገልጋይ መሆኔና ይህን ሁሉ በትእዛዝህ እንዳደረግሁ ዛሬ ይታወቅ። 37ይህ ሕዝብ፣ አንተ አምላክ እግዚአብሔር እውነተኛ መሆንህንና ልባቸውን የመለስኸው አንተ መሆንህን ያውቁ ዘንድ እባክህ ስማኝ፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ እባክህ መልስልኝ።”

38ከዚያም የእግዚአብሔር እሳት ወርዳ መሥዋዕቱን፣ ዕንጨቱን፣ ድንጋዩንና ዐፈሩን ፈጽማ በላች፤ በጕድጓዱ ውስጥ ያለውንም ውሃ ላሰች።

39ሕዝቡም ሁሉ ይህን ሲያዩ፣ በግንባራቸው ተደፍተው፣ “አምላክ እግዚአብሔር እርሱ እውነተኛ ነው! እግዚአብሔር እርሱ እውነተኛ አምላክ ነው!” አሉ።

40ከዚያም ኤልያስ፣ “የበኣልን ነቢያት ያዟቸው! አንድም ሰው እንዳያመልጥ” ሲል አዘዘ፤ ሕዝቡም ያዟቸው፤ ኤልያስም ወደ ቂሶን ወንዝ አውርዶ አሳረዳቸው።

41ኤልያስም አክዓብን፣ “የከባድ ዝናብ ድምፅ ይሰማልና ሂድና ብላ፤ ጠጣም” አለው። 42ስለዚህ አክዓብ ሊበላና ሊጠጣ ሄደ፤ ኤልያስ ግን ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ጫፍ ወጣ፤ ፊቱንም በጕልበቶቹ መካከል አድርጎ ወደ መሬት አቀረቀረ።

43አገልጋዩንም፣ “ውጣና ወደ ባሕሩ ተመልከት” አለው።

አገልጋዩም ሄዶ ተመለከተና፤ “በዚያ ምንም የለም” አለው።

ኤልያስ ሰባት ጊዜ፣ “እንደ ገና ሂድ” አለው።

44በሰባተኛው ጊዜ አገልጋዩ፣ “እነሆ፤ የሰው እጅ የምታህል ትንሽ ደመና ከባሕሩ እየወጣች ነው” አለው።

ኤልያስም፣ “ሂድና አክዓብን፣ ‘ዝናቡ ሳያግድህ፣ ሠረገላህን ጭነህ ውረድ’ ብለህ ንገረው” አለው።

45ወዲያውኑም ሰማዩ በጥቍር ደመና ተሸፈነ፤ ነፋሱ ነፈሰ፤ ከባድ ዝናብ ጣለ፤ አክዓብም በሠረገላ ተቀምጦ ወደ ኢይዝራኤል ሄደ። 46የእግዚአብሔርም ኀይል በኤልያስ ላይ ወረደ፤ ኤልያስም ልብሱን ከፍ አድርጎ በቀበቶው ካጠበቀ በኋላ፣ እስከ ኢይዝራኤል ድረስ አክዓብን ቀድሞት ሮጠ።

Copyright information for AmhNASV